የቱን ልመን?
|
እንደምን ከርማችኋል አንባቢዎቼ የትጠፋህ አትበሉኝ እንጂ ዛሬ ብቅ ብያለሁ።አይ የኔ ነገር ፥ ተናፍቄ እንደሁ ብዬ እኮ ነው ማንነቴን ሳልገልጽ የትጠፋኸ አትበሉኝ የምለው።ለካስ የመጠፋፋት ማግስት ናፍቆት ፤የናፍቆት ሰልስት ደግሞ መረሳሳት ነውና እረስታችሁኝም ይሆናል።ለማንኛውም ማነህ ካላችሁኝም አላሚው ነኝ።ያአለቃ እምባቆም ተማሪ የሆነው የህልም ፈቺው ወዳጅ።ዛሬ ህልም ሳይሆን የእውን ቅዠት ይዤ ስለቀረብኩ ህልም ፈቺው ወዳጄን አልጠራሁትም።ጨዋታዬ ከናተው ጋር ነውና አብራችሁኝ ቆዩ። መቼም ያለፉት ሁለትና ሧስት ወራት ሃገራቸን ውስጥ የተፈጸመውንና እየተፈጸመ ላለው ነገር አዲስ የሚሆን ያለ አይመስለኝምና አልመለስበትም።የኔ ትኩረት ምን ለምን በማን ተከወነ የሚለው ላይ ይመስለኛል።ቅዠት ነውና ስሳሳትም ቀስቅሱኝ። ወያኔ ተከፋፈለ አሉን።በጄ ብለን ገና ለምን የሚለውን ጥያቄ ሳንሰነዝር ክፍልፋዮቹ የክፍፍሉን ምክንያት በየበኩላቸው አቀረቡልን።አዥጎደጎዱልን።ለወትሮው አጥራችው አጠገብ የማያስደርሱን ሰዎች ዛሬ ጓዳቸውን ምስጥራቸውን ገልብጠው ሲያሳዩን ቢገርመንም አሁንም በጄ ከማለት በስተቀር ምንም ማለት አልተቻለም።ብቻ እነሱ ተካሰሱ ተዋቀሱ ።አንዱ ወገን የጸባችን ምክንያት ማጀታችን አለመጠን በመጥበቡ ሰፋ ያለ ቤት እንከራይ ስንል ጥቂቶች ከጠባብ አንወጣም ማለታቸውና የግል ጥቅም አግበስባሽነታቸው ይጣራ መባሉ ነው አለን። ሌላውም ደግሞ የጸባችን መንስኤ የሃገር ጥቅም አሳልፈው ለመስጠት የፈለጉትን ሰዎች በመቃወማችን ነው በማለት አስረዳን። የግል ጥቅም የሚያግበሰብሱትን ላጋልጥ ስል ነው ጸቡ የተነሳው ያለን ክፍል የግል ጥቅም ፈላጊዎች በተባለው ክፍል የሃገር ጥቅም አሳልፎ ሰጠ ተብሎ ሲነገረን ደግሞ የቱን እንመን ? የሃገር ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀ ከቶውኑ እንዴት የግል ጥቅም ፈላጊዎችን ሊያጋልጥ ይቻለዋል? የግል ጥቅም የሚያግበሰብስስ እንዴት ለሃገር ጥቅም ተሟጋች ይሆናል? ብዬ እራሴን ጠየኩ ። ግራ የግባው ነገር።ጎተራ ዘራፊው ቁና ሰራቂውን እፋረዳለሁ ሲል ቁና ሰራቂው ጎተራ ጠባቂ ነኝ ሲለኝ የቱን ልመን? አውጣሁ አወረድኩ ሁለቱም ውሸት አይሆንም ። ከሁለት አንዱ ብቻ እውነት ነው ብሎ ለመቀበል ያዳግታል።ምክንያቱም ጎተራው ጎድልዋል ተዘርፏል። ስለዚህ በቁናም ተዘረፈ ወይም ሙሉ ለሙሉ ተዘረፈ ሌባ አለ ማለት ነው።ጎተራውን ሙሉ ለሙሉ አሳልፎ ሊሰጥ ያሰበው ጠባቂ ቁና ሰራቂዎችን አጋልጣለሁ ማለቱ አልተዋጠልኝም እንክዋን ለአንድ ቁና ለጎተራውም አልሳሳምና።ቁና ሰራቂው ግን ጎተራ አዘራፊውን መቃወሙ ሊሆን አይችልም ማለት አቃተኝ።ለምን ቢባል በቁናም ሊሰርቅ የሚችለው ጎተራው እስካለና የጎተራው ጠባቂ እስከሆነ ድረስ ነውና የጎተራው ሙሉ ለሙሉ መምዋጠጥና መዘረፉን አይፈልግም። ስለዚህ ሁለቱም እርስ በእርስ የሰነዘሩት ክስ ትክክል ይመስላል።ይህ የሚያሳየው የዘራፊና የልክስክስ ሌባ ክርክር መሆኑን ነው። ያማለት ደግሞ ሁለቱም ወገን ለእምነት አይበቃምና ጎተራ ከመጠበቅ ሃላፊነት መነሳት አለበት። ግን ሌላ ብረት አንጋች ጠባቂ የለምና ከሁለት አንዱ ወደስራው መመለሱ የግድ ነው ተብሎ ምርጫ ቢሰጠኝ የምመርጠው ቁና ዘራፊውን ነው ቀለብተኛውን ለከፋ ረሃብ የሚጎዳው ዘራፊው ነውና።ያም እድል ለቀለብተኛው አልተሰጠም ቁና ዘራፊው አቅም አጥቶ ተሸነፈ።ዘራፊው ጥበቃውን ቀጠለ። አንድ ያልገባኝ ነገር ብዙዎቹ ቁና ዘራፊዎች ከጎተራ ዘራፊው ጎን ሆነው ሌሎቹን ቁና ዘራፊዎች መውቀሳቸው ነው። እንደቀለብተኝነቴ ሠጋቴ ጎተራው ባዶ ሆኖ ለባሰ ረሃብ ተጋልጨ በገዛ ዳቦዬ ልብልቡን አጣሁት እንዳይደርስብኝ ነው።
የጎተራውን ምሣሌ በዚህ ላብቃና ወደሌላው ቅዠቴ ልሸጋገር። የወያነን አመራሮች ክፍፍል ጉድ ጉድ ስል የተማሪዎች የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው በጥይት ተቆሉ።የናንተ የውድ ህዝበ ጥቅም ለማስከበር ስል ከግል ጥቅም አግበስባሾችና ከጠባቦች ተጣላሁላችሁ ዳሲለን የነበረው መከታችን የአቶመለስ ቡድን የህዝቡን ልጅ በአደባባይ በባሩድ ጠበሰው።ለምን ሲባል ኢሃድግ ተዳክምዋል በሚል ሰበብ የተነሳውን ውዥንብር አከሸፍኩ አለን።ግራ የሚያጋባ ነገር። ግን ወደ እውነቱ የተጠጋ ሆነ።ቀጠለ ተማሪዎችን ቀስቅሳችኋል ብሎ ፕሮፌሰሮችን አሰር።ወዲያው የፕሮፌሰር መታሰር የሚጭረውን እሳት ውሃ ሊያፈስበት አስቦ የደርግ ባለስልጣናትን ለቀቅኩ አለን።ማንም ይሁን መለቀቁ ያስደስተኛል።ይሁንና የደርግ ባለልጣናት ለቆ ፕሮፌሰርን ማሰር ተራ የማካካሻ ዘዴ በመሆኑ የሚያደርጉትን እንዳጡና ተንኮልም እንዳለቀባቸው አሳየኝ። አሁንም አንድ የመለስ ቀኝ እጅ የተባሉ ሰው በአንድ የወያኔ ሻለቃ ተገደሉን ሰማን።በዚህም አዘንኩ ማንም እንዲሞት አልሻም።ወያኔ በግለሰቡ ሞት ከተሰማው ሃዘን የበለጠ ያስጨነቀው የምዋችና የገዳይ ጸብ የወያኔ የውስጥ ችግር አካል ነው።የሚል ግንዛቤ ሊያመጣ ይችላል የሚለው ሠጋት በመሆኑ የግድያው መንስኤ የግል ጸብ ነው በማለት ግለሰቡን የገደላቸውም የአቶ መለስ ደጋፊ መሆኑን ነጻ በሚባሉት ጋዜጦች በነ ጦማር አስነበበን።ነገሩ እውነት ሊሆን ይችላል። የገረመኝ ወሬውን ለመዘገብ ጦማር ከኢሃድግ ጋዜጣ ከሪፖርተር ቀድሞ ማገኘቱ ነው።ይህ ደግሞ ሌላ ጥርጣሬ አይፈጥርም ብላችሁ ነው።ጦማርም ተለጣፊ ጋዜጣ ይሆን ከሆነስ ለምን አዘጋጆቹ በየጊዜው ይታሰራሉ? ቅዠታም ነኝና ቃዥቼ ሊሆን ይችላል ብቻ ልቀጥል አትሰልቹኝ ስሙ፥ የወያኔ ካድሬዎች በር ለበር ዞረው ድምጽ ሰብስበው ለስልጣን ያበቋቸውን የትናት ታጋዮች የዛሬ አፈንጋጮች ዛሬም በር ለበር እየዞሩ በሰበሰቡት ድምጽ አወረዷቸው።ህዝቡም እምነት አጣባቸ ተባልን። እውነት ህዝቡ ብሎ ከሆነ እቀበላለሁ።ግን አይመስለኝም የትግራይ ህዝብ እምነት ያጣበትን ከልቡ እንዲናገር እድል አግኝቶም የሚያውቅ አይመለኝ።እስከማውቀው ድረስ የትግራይ ህዝብ እርቀ ሰላም ይውረድ ባይ ነው።ግን አልሆነም። በአንድ ወቅት ኮለኔል መንግስቱ በሃገሪትዋ ሰለም እንዲሰፍን ከተቃዋማዎች ጋር ይቅር ለእግዚአብሄር ተባባሉ የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው ፥ይህ የሃገር ጉዳይ እንጂ እንደ ባልና ሚስት ጸብ ይቅር ተባባሉ ሊባል አይገባም በሚል ዳቁዴሣ መመለሳቸውን አስታውሳለሁ።የስልጣን ጉዳይ ለድርድር ማቅረብ አፍሪካ መሪዎች አይዋጥምና ዛሬም አቶ መለስ እርቀ ሰላም ይውረድ የሚለው የትግዳራይ ህዝብ ፍላጎት እንዳልተዋጠላቸው ጠየም አድርገው የገለጡባት ከፕሬዘዳንት ነጋሶ ለቀረበው ተመሳሳይ የእርቅ ሃሳብ በሰጡት ለተፈጠረው ሉዩነት እርቀሰላምን እንደመፍትሄ ማቅረብ በወያኔ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት ነው በሚል መልስ ነበር።እነ አቶ ካሡ ኢላላና የአማራው ክልል ፕሬዘዳንት አቶ አዲሱ ለገስ ከአቶ መለስ ጎን በመቆም የተወገደውን ቡድን ጎጠኛና ሙሰኛ ብለው መውቀሳቸው ግን በአቶ መለስ አገላለጽ በህዋት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ተብሎ አልተወሰደም።ከዚህ የተረዳሁት ህዋት በአቶ መለስ ወንበር ሠር መሆንዋን ነው። ወንበሩን የደገፈ በህዋት ውስጥ እንደፈለገ ወጣ ገባ ማለትና ጣልቃ መግባት ብቻ ሳይሆን ማደርም ይፈቀድለታል።ወንበሩን በእርቀሰላም ለድርድር የሚያቀርብ ግን ጣልቃ ገብ ነውና አድብ ይባላል። መቼም ቅዠቴ ብሎ ሳይሰለቻችሁ አይቀርምና።ወደ መደምደሚያዬ ላምራ።ከሁሉም ያንገበገበኝ የለጋ ወጣቶች በጥይት መቆላት ነው።የቅዠቴም መሰረት እሱነውና የነዚ የንጹሃንን ደም ያፈሰሰም ሆነ እንዲፈስ ያደረገው አካል ለፍርድ የሚቀርብበትን ቀን ያቀርበው ዘንድ በጸሎት እንተጋ ዘንድ ይዣችህዋለሁ። እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ያስባታል።በሌላ ቅዠትም ሆነ ህልም እስክንገኛኝ ክፉ እልም እልም እያልኩ የምሰናበታችሁ የናተው አላሚው ነኝ ከደቡብ ምስራቅ ክፍለ አለም
|