Articles                                                 መጣጥፍ

  Back Home      Articles          Poems           News              Jokes               Email Us

        THIS WEBSITE IS CURRENTLY BLOCKED IN ETHIOPIA

Democracy For Ethiopia Support Group


 

PO Box 2227, Footscray Vic, 3011              

     ያመለጡን ዕድሎችና የቀሰምናቸው ትምህርቶች

ግልፅ ደብዳቤ  --- ለቅንጅት ፓርቲና ለህብረቱ አመራሮች፡

ከዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ የድጋፍ ኮሚቴ

ሜልበርን -- አውስትራሊያ

ውድ የቅንጅትና ኢዴኃህ መሪዎች፣

 

ከምርጫው ቀደም ብሎና  በምርጫው ወቅት ህብረታችሁን በማጠናከርና በጋራ በማስተባበር ያካሄዳችሁት ትግል ለኢትዮጵያ ህዝብና ለወገናችን በሙሉ ከፍተኛ ተስፋና ብርታት ሰጥቷል።  በዚህ ወቅት ያሳያችሁት የላቀ  ድርጅታዊና  ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ : ለሠላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ መንፈሳዊ ንቃትና ጥንካሬን ሰጥቷል።   ለሃገራችን የወደፊቱን የተረጋጋ ሰላማዊና የብልፅግና ጎዳና  ብሩህ አማራጮችን ያመላከተም ነበር። ስለሆነም በአያሌው በታዩት አመርቂ ተግባሮቻችሁ ኮርተንባችኋል። የሁንና በቅርቡ ከተከሰቱት ሁኔታዎች አኳያ የታዩንን ችግሮችና የተሰሙንን ቅሬታዎች ለመግለፅ እንወዳለን።

እኛ በሜልበርን / አውስትራሊያ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን  የዳር ተመልካቾች ወይም ታዛቢዎች ሳንሆን በሃገራችን የዴሞክራሲ ትግል ውስጥ በቀጥታ እየተሳተፍን ያለን ነን። አቅማችን በፈቀደውና በሙሉ ልብ በመንቀሳቀስ የተቃዋሚ ሃይሎች / ህብረቱም ሆነ ቅንጅቱ / ገና ሲመሠረቱ ጀምሮ በገንዘብ፤ በዲፕሎማሲና በሞራል ድጋፍ እየሰጠን የምንገኝ ነን። ለዚሁ ድጋፋችንና ትብብራችን አንዱ ምሳሌ  -- በኦሊቪያ ሮሴት -- ተቀናብሮ በአውስትራሊያው  የኤስ ቢኤስ/
SBS ቴሌቪዢን የቀረበውን፤ በግንቦቱ 7 ምርጫ ላይ ያተኮረ ፤ ዶኩሜንታሪ ዘገባ ፤ የኛን ጥረቶች የሚያመላክት ነው።

ምንም እንኳን በአካል ውጪ ሃገር የምንገኝ ቢሆንም፤ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የህዝብ ወገንና ሃገር ወዳድ ሁሉ የዴሞክራሲ ትግሉ አካልና አጋር ነን ብለን እናምናለን። በወያኔ አምባገነን መንግሥት፤ በሃገራችን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥና በምርጫ እንዳንሳተፍ ብንታገድም ኢትዮጵያዊ ዜግነታችንና የትውልድ መብታችንን የሚነጥቀን ማንም ሃይል አይኖርም።

ስለሆነም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወገናችን፣ እንደ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሁሉ ስለወቅቱ ሃገራዊ ትግልና አካሄዱ የምንሰጠው አስተያየት ጠቃሚና ክብደት የሚሰጠው ይሆናል ብለን እንገምታለን።

ይሁንና ፣  እንደ ወያኔ መንግሥት ያለ ጨካኝ አገዛዝን ለሚታገል ሁሉ በትግሉ መንገድ ላይ፤ አንዳንዴም ጎጂ የሆኑና የማይታለፉም ስህተቶች ሊፈፀሙና ሊከሰቱም እንደሚችሉ የምንጠ ብቀው እንጂ እንግዳ ነገር የሚሆንብን አይደለም። ስለሆነም ሃላፊነት በተሞላው አያያዝና ገንቢ ውጤቶችንም ለማግኘት ተፈፀሙ የምንላቸውን ስህተቶችና ድክመቶች መጠቋቆሙና ፤ ከነሱም ተምሮ ቀጣዩን እርምጃ ውጤታማ እንዲሆን መጣሩ ከወገን ሁሉ የሚጠበቅ በጎ ተግባር በመሆኑ በዚህ መንፈስ በቅርቡ ያየናቸውንና ተከሰቱ ብለን የምናምነውን ጉድለቶች በአክብሮት ለመጠቆም እንወዳለን።  

1/ ከምርጫው ወዲህ ወደ ፓርለማ እንግባ/ አንግባ በሚለው ሃሳብ ላይ በየአካባቢው በከፊልም

ቢሆን ከመረጣችሁ ህዝብ ጋር ሁለቱም ድርጅቶች  ውይይት ማካሄዳችሁ የሚታወስ ነው። በነዚህ ውይይቶች የህዝቡ ፍላጎት ያለማወላወል - በተጭበረበረ  ድምፅና ህገ - ወጥ በሆነ መንገድ በተቋቋመ የወያኔ ፓርለማ መግባት የለባችሁም የሚለውን - ሃሳብ አስረግጦ ገልፆላችኋል። ከዚህም በበላይ ለማንኛውም አስፈላጊ ትግል ህዝቡ ከጎናችሁ ሆኖ ድጋፉን እንደሚሰጥ በማያወላዳ መንገድ ገልጿል።  ለዚህ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ትግል ለምትወስዱት ውሳኔ ሁሉ፤ ቀደም ብሎ እንዳሳየውም  ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመብቱና ለነፃነቱ ለመክፈል መዘጋጀቱን አሳውቋችኋል። ይሁንና አሁን እንደታዘብነው ገና ከምርጫው ማግሥት ጀምሮ የወሰዳችኋቸውን እርምጃዎች ስንመለከት፣ ትኩረታችሁ ከመለስ ጋር መደራደርን እንደ ዋና ዓላማ የያዘ እንጂ፣ በምርጫው የተገለፀውን የህዝቡን ፍላጎት ለማስፈፀም ህዝቡን እያሳተፋችሁና እያማከራችሁ የቀጠላችሁት ትግል አልነበረም ማለት ይቻላል።

በመሆኑም ተደናግጦ የነበረው መለስ ፋታ በማግኘት፣ ይበልጥ የናንተን አጀንዳ መቼና እንዴት መደራደር እንዳለባችሁ ወሳኝ ለመሆን ዕድል ተሰጥቶታል። ቀስ በቀስም የራሱ አጀንዳ የሆነ ውን ወደ ፓርለማ የመግባት ጥያቄ ዋናው የተቃዋሚውም አጀንዳ እንዲሆን አድርጓል።

በአንፃሩ ተቃዋሚዎች ከመስከረም ቀደም ብሎ የህዝቡን ድጋፍ፤ ድምፅና አስተያየት በመከተል ተጉዘው ቢሆን ኖሮ የአጀንዳዎችን ዓይነትና የድርድሮችን ይዘት ለመወሰን የሚችሉበት አቋም ይኖራቸው ነበር።

2/ እንደሚታወቀው የህዝቡን ትግል የሚመራ አካል የመራጩን ህዝብ ዓላማና ፍላጎት ግልፅና በማያሻማ መንገድ ከራሱ ዕቅዶችና ስልቶች ጋር ማዛመድ ይጠበቅበታል።ይሁንና፣ አሁን እንደታየው የተቃዋሚ ሃይሎች አመራሮች፤ የህዝቡ ዓላማ የሆነውን በሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ የተቃውሞ ትግል የወያኔን መንግሥት ከሥልጣን ለማስወገድ የሰጠውን ድምፅ ወደ ጎን በማድረግ ወይም በግልፅ ሳይቀመጥ፣ ድርድር መግባቱ ስህተት ይመስላል።

የህዝቡን ሃይልና ቁርጠኛ ውሳኔ ተጠቅመው ዋናውን ዕቅድ / ወያኔን ማስወገዱን / ሳይሆን የድርድር ዕቅድን አስቀድመዋል የሚል እንደምታ ፈጥራችኋል። በግልፅ ለማስቀመጥ፣ ባለፉት ጥቂት ወራት እንደታዘብነው  የሃገራችን ተመክሮ እስካሁን የነበሩትን የብዙሃን እንቅስቃሴዎች  ታሪክ  መሠረታዊ ይዘት በራሱ ያቆመና  ያገላበጠ ነበር ቢባል  ማጋነን አይሆንም።

በቅርቡ የተከሰተው፣ ተቃዋሚ ሃይሎች ከህዝብ ቀድመው የትግሉን አቅጣጫ እያመላከቱ  አመራር ሲሰጡ  ሳይሆን፣ በአንፃሩ ህዝቡ ቀድሞ መሪዎች  ተከታይ  የሆኑበት  ዕንግዳ ሁኔታ  ነበር። መለስ በህዝብ ሃይል ካልተገደደ በቀር፣ በውዴታና በፍላጎት እንኳን ሥልጣኑን አሳልፎ ሊሰጥ ይቅርና ማጋራትም የሚቀበል አይደለም። ለአምባገነኑ መለስ፣ ቅንጣት ታክል የሥልጣኑን ጫፍ እንኳን የምተነካ ሰላማዊ ድርድርም ሆነ ሃሳብ ከተመለከተ ወደ ለመደው የሃይል እርምጃ ለመሄድ የሚያነሳሳው ምልክት አድርጎ ነው የሚያየው። እንዲህ ያለ አምባገነን፣ በህዝብ ሃይል ተገድዶ  ብቻ ነው  የግንቦት 7ቱን የህዝብ ድምፅ የሚያከብረው። በአንፃሩ ደግሞ፣ ህዝቡ የግንቦቱን የድምፅ  ውሳኔውን  በቃል ብቻ ሳሆን በተግባሩ፣ ባልተቋረጠ ሰላማዊ የህዝብ ትግል መለስን ከሥልጣኑ ለማስወገድ፣ በቁርጠኝነት ተነሳስቷል። እያስመሰከረም ይገኛል።

3/ የመለስ ቡድን፣ አብዛኛውን የተቃዋሚዎች የስብሰባ ዕቅዶች፣ በአዲስ አበባና  በሌሎችም ቦታዎች ሊደረጉ የታሰቡትን፣ ሁሉ አግዷል። አባሎቻቸውን በገፍ ያሥራል፣ ያሰቃያል፣ እየገደለም ነው። የተቃዋሚ መሪዎችን በተደጋጋሚ አስፈራርቷል፤ ጉዳት ሊያደርስ እነድሚችልም ዝቶባቸዋል። በዕብሪትም ለነሱ ያለውን ንቀት እስካሁን እየገለፀ ይገኛል። በአደባባይና በግልም እንደገለፀው፣ ከተቃዋሚ  መሪዎች ጋር  በዋነኞቹ ነጥቦች፤  ማለትም የህዝቡ ድምፅ መጭበርበሩን በተመለከተ፣ በጊዚያዊ ብሐራዊ የአንድነት መንግሥትና በተያያዙ ጉዳዮች ላይ --ለመወያየት ምንም ፍላጎት እንደሌለው በተደጋጋሚ አሳውቋል። በዚህም አቋሙ ቀጥሏል።

4/ በአንፃሩ የመስከረም 22ቱ የህዝብ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ከተላለፈ በኋላ፣ የመለስ መንግሥት በመከልከሉና ሽብር ለመቀስቀስ በመሯሯጡ፣ ጥሪው ተሰርዟል። ይሁንና ድንገት መለስ እምቢ ቢል እንኳን ምን መጠባበቂያና አማራጭ ዕቅድ ተዘጋጅቶ እንደነበር የተገለፀ ነገር ባለመኖሩ፣ ቢያንስ በግምት ውስጥ መግባት የነበረበት አማራጭ እንዳልተያዘ መረዳት

ችለናል።

አሁን  ሁኔታው ካለፈ በኋላ፣ ወደኋላ መለስ ብለን  ስንመለከት  ግልፅ  የሆነልን ቢሆንም፤  የፈለገው ዝናብና ዶፍ ቢወርድም የመስከረም 22ቱ የስብሰባ ጥሪ እንደማይታጠፍ የነበሩት  ምልክቶች ሁሉ  ይጠቁሙን  ስለነበር፤  በድንገት በመለስ እምቢተኝነት ተሰርዟል  ሲባል፣  በእጅጉ ግር አሰኝቶናል፤ አደናግሮናል።

5/ በተጨማሪ - በሠዓታት ልዩነት  የተጠራውን  “ የሥራ ማቆምና ከቤትህ ተከተት “ ጥሪ በመሰረዝ /በማጠፍ - መለስ ለባዶ የጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር ተስማምቷል ተብሎና ይህንንም ውጤት - አልባ እርምጃ እንደድል  በመቁጠር  የምሥራች እስከ መባባል መደረሱ በጣም አሳዝኖናል።

መለስ ለድርድር መቅረቡ ብቻ /ምን ዓይነት ድርድር እንኳን እንደሆነ ሳይታወቅ/ የፖለቲካ ጨዋታው  ዋና ግብ  ተደርጎ  መታየቱ፤ የህዝቡ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎችን  ተክቶ መቅረቡ ፈር የለቀቀ ሆኖ ታይቶናል።

የተቃዋሚ ሃይሎች መሪዎች፣ ቢያንስ ቢያንስ ከማንኛውም ድርድር በፊት፣ በአስቸኳይ የእስረኞች መፈታትን፤ በአባሎችና ደጋፊዎች ላይ እየተካሄደያለው ሽብርና ማንኛውም ተፅዕኖ እንዲቆም እንኳቅድመ ሁኔታ፣ ከሥራ ማቆሙ አድማ -ሰረዛ በፊት፣ መቅረብ የነበረበት ይመስለናል።

6/ የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ፣ መንግሥታትና ደርጅቶች አመለካከት፣ አሁን ባለው ሁኔታ ላይ የማይናቅና ቁልፍ ሚናን እንደሚጫወት የማይታበል ሃቅ ነው። ይሁንና በሃገራችን ለሚደረግ ትግልና ለውጤቱ  ዋናውና ወሳኙን ሚና የሚጫወተው ህዝቡ፣ ዜጋው እራሱ ብቻ ሲሆን፣ የዓለም  አቀፍ ህብረተሰብ አጋዥና በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ አስተዋፅዖ ነው ሊኖረው የሚችለው።

በአጠቃላይ መልኩ እንደታዘብነው ግን መሪዎቻችን ከልክ በላይ ክብደት ለዓለም አቀፍ ማህበረ ሰብ መንግሥታት፣ ዲፕሎማቶችና / በተለይ ለለጋሽ ቡድን ድርጅቶች / በመስጠት፣ በነሱ ተፅዕኖ ወደ መመራት ያዘነበላችሁበት ሁኔታ ተከስቷል። በሌላ በኩል፣ መለስ ግን በነሱ ግፊትና ተፅዕኖ ቅንጣት ታክል እንኳን አቋሙን እንዳልቀየረ፣ የውሸት ተስፋ  እየሰጣቸውና የገባቸውን “ቃሎች”

እንኳን ተግባራዊ ሳያደርግ እየቀጠለ እንደሆነ እያየን ነው።

ውድ  የተቃዋሚ  ሃይሎች  መሪዎች !

ከላይ ከዘረዘርናቸው ግንዛቤዎችና ትዝብቶች ስንነሳ  ሁለት አበይት ቁምነገሮችን እንማራለን።

አንደኛ፣ ልንገነዘበው የሚገባ ትምህርት፣ በሃገራችን የሚካሄደው ዴሞክራሲያዊ  እንቅስቃሴ የህዝብን ዋነኛ ፍላጎትና ዓላማ የሆነው በግንቦት 7ቱ ምርጫም እንደተረጋገጠው የወያኔን አምባገነን መንግሥት ጠራርጎ ማስወገድ ነው። ስለሆነም  የቅንጅት ፓርቲና የህብረቱም ተቀዳሚ ዓላማ ይህንኑ የሚያንፀባርቅ ሊሆን የሚገባው ነው።

 ሁለተኛ፣  የህዝቡ አስተያየቶች፣ ዓላማቆች መሪዎቹ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች፣ ዘዴዎቻቸውና      ሥልቶቻቸው ውስጥ ተካተው ከህዝቡ መሃል የሚገኙና የእንቅስቃሴው አካል የሆኑትን ማህበረሰባዊ / civic / ድርጅቶችን አስተባብሮና በአንድነት ተባብሮ በጋራ በምክክርና በቅንብር  ተግባራዊ እንዲሆኑ መጣር ነው።

       ከላይ የተጠቀሱት ተመክሮዎችና ትምህርቶች ለወደፊቱ ትግላችን አካሄድና ድል መምታት ጠቃሚ ቦታ ይኖራቸዋል ብለ ተስፋ እናደርጋለን።

በመጨረሻም፣ ምንም እንኳን ጥቂት የህብረቱ አባል ድርጅት መሪዎች ፣ከአብዛኛው ውሳኔ ውጭ ፓርላማ በመግባት፣ ቅር ቢያሰኙንም፣

በቅርቡ  በቅንጅት ፓርቲ  የተገለፀው አጠቃላይ  የሥራ ማቆምና  የክተት ጥሪ ዝግጅት፤ እንዲሁም በህብረቱ የወጣው የዳግም ትግል ጥሪ መግለጫ -- በጣም የሚያበረታታና ጥሩ አቅጣጫ የያዘ መሆኑን እንገምታለን። በርቱልን።

ለሚደረገው ማንኛውንም አይነት ተሳትፎ የበኩላችንን ግዴታ ለመወጣትና ከጎናችሁ ሆነን የጋራ ትጋላችንን ለማጠናከር ደግመን ቃል እንገባለን። ቀጣይ ድጋፋችንና ትብብራችንንም ለሁለታችሁም፣ ለቅንጅት ፓርቲና  ለህብረቱ  እንደወትሮው በሃገር ወዳድነት መንፈስ እናጠናክራለን።

የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔን አምባገነን ሥርዓት ያለጥርጥር ያስወግዳል።

ኢትዮጵያ  ለዘላለም  ትኑር !

ጥቅምት 17, 1998 ዓ.ም.