|
(ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገ /መድህን እንዳስረዱት) እንቁ" (Jewel) ከሚሉት የከበረ ድንጋይ ሠም የተወረሰ ሲሆን "ጣጣ" ደሞ ያው መከራ ማለት ነው። ለአዲስ አመት አደይ አበባ እንደ እንቁ ምሣሌ ናት። ውብ ቆነጆ የምታባባ እንቁ ናት። በተለይ በችቦው የአናት አበባዎች ዳናት ላይ እንደ ፈርጥ የምትቀመጠው ነጭ ሶሪት አበባ የደማቁ ጸሓይ( ኦራ) ምልክት ናት።ከአደይ አበባው ጋር ለመስዋት ተበርክታ ትቃጠላለች። እንቁ ሆይ ጣጣሽ ደረሰ የምትባለው ለዚህ ነው። ክረምትና ጎርፍ ተከታትሎ ወንዝና ጅረት ሞልቶ አባይ እንደ ሰንጋ ፈረስ አጀብ ተጥለቅልቆ ወደ ምድረ ግብጽ ሲወርድ የጭቃውና የማጡ ጨለማ ወራት አልፎ የአዲስ ዘመን ምሠራች ብርሃን የሚፈነጥቅበት መስከረም ሲፈካ አደይ አበባ በእልልታና በሆታ ለመስዋትነት ትበስራለች። እንቁጣጣሽ እንደ ውብ ለጋ የምታባባ ወጣት ድንግል ልጃገረድ ተምሳል ነች። ለመስዋትነት ስለምትቀርብ ግን( አዬ እቴ አበባዬ እቴ አበባ ስትለኝ ከርማ ጥላኝ ሄደች በሃምሌ ጨለማ) እየተባለች ሃዘንና ደስታ በተመሳቀለበት ሁኔታ ትሸኛለች። ሃዘን ለሷ እልልታ ለአዲስ ዘመን ጸሓይ ይበስራል።
የዛሬ 6139 አመት ካም አበው ጥቁር ግብጻውያን አበቅቴን ለአራት ከፍለው በምጸው ፤ በበጋ ፤ በበልግና በክረምት
ለይተው በአለም ለመጀመሪያ ጊዜ ከደነገጉ ጀምሮ ከብዙ አመታት በኋላ ኦሪት ክርስትናና እስልምና በየመነሻ ልደቶቻቸው
አዳዲስ የቀን መቁጠሪያ ቢቀይሱም እንኳ መነሻ መሰረታቸው በአባይ ወንዝ መሙላትና መጉደል ላይ የተመሰረተ የካም አበው
ግብጻያን ጥበብ መሆኑን አልካደም። የኛም የዘመን መቁጠሪያ ከዘመን ወደ ዘመን ትንሽ ይቀያየር እንጂ መነሻ
መሰረቱ ይኸው የአባይ ስልጣኔ ተብሎ የሚታወቀው የካም አበ መዋቅር ነው።
|