Articles                                                 መጣጥፍ

  Back Home      Articles          Poems           News              Jokes               Email Us

        THIS WEBSITE IS CURRENTLY BLOCKED IN ETHIOPIA


አሚውና እልም ፍቺው
 

                                       
       

እንደምን አላችሁልኝ የቋጠሮ ገጽ እድምተኞች። እኔ ደህና ነኝ። ረስታችሁኝም ከሆነ አልፈርድባችሁም ከተገናኘን ሰንበትበት ሳይል አልቀረም። ወቸ ጉድ ምን ሰንበትበት ብቻ እንዲህ አይነት ቃል የለም አትበሉኝ እንጂ አመትመትም ሳይል አልቀረ። መቼም የግዜው አበራረር እንደ አፍሪካ መሪዎች ላንድ ክሩዘር ነው።ምክንያቱ ያልገባኝ የግዜው መብረር እንጂ የአፍሪካ መሪዎችማ አምባ ገነንነታቸው ካፈራባቸው እልፍ አእላፍ ጠላቶቻቸው ጥይት ለማምለጥ ነው መብረራቸው። ጨዋታ አማረልኝ ብዬ ስዘባርቅ እራሴን ማስተዋወቁን ዘነጋሁት።

አዎ እኔ አላሚው ነኝ። ከአመት በፊት ይመስለኛል በዚሁ በቋጠሮ ገጽ ላይ ህልሜን ይዤ ቀርቤ ነበር። ታስታውሱ እንደሆን ህልሜን የፈታልኝ የአለቃ አምባቆም የቅኔ ተማሪ ነበር ። ታዲያ ህልም ፈቺው አንድ ግዜ ብቻ ህልሜን ፈቶልኝ ዳግም ህልሜ ካቆመበት ቀጠለ ና ፍታልኝ ብለው። አይ ይህ ቅዠት እንጂ ህልም አይደለም ህልም እንደ ዘመኑ የአቡዠዲ ግርግር እንደ ሲኒማው ካቆመበት ቀጥሎ አግኝቼ ፍቺውን ሰጠሁ ብዬ ለአለቃ አምባቆም ብነግር ድቁናዬን ገፈው አቆፋዳዬን ነጥቀው ከ አለም ብላሽ እንደሚመድቡኝ አውቃለሁና አላደርገውም አለኝ። ብቻ እንደምንም እኔም የቋጠሮ እድ ምተኞቼም ለምነውት የቀጠለውን ህልሜን ፈታልኝ። ዛሬም በምስጥር ጠርቼው ህልሜን ሊፈታልኝ አብሮኝ አለ። ብቻ አሁንም አለቃ አምባቆም ጆሮ እንዳይገባ ይሰጋልና ስሙን በደፈናው ህልም ፈቺው ብለን እንጥራው።

የሚገርማችሁ ዛሬም ከ 3 መንፈቅ በፊት ያለምኩት ህልም ቀጣይ ነው። ብቻ ቅዠትም በሉት ቅብዠት ልተንፍሰው ፈቺውም ፍቺውን ይሰንዝር።

ለጥ ያለ ሜዳ ላይ ያለሁ ይመስለኛል። ባሻገር ከወንዝ ወዲያ ማዶ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚንቦገቦግ መንታ እሳትና የጭንቅ ጩኸት ይሰማኛል።ወዲህ ማዶ እኔ ያለሁበት ሜዳ ላይ ብርሃን ሆኖ ከወንዝ ወዲያ ማዶ ጨለማ መሆኑ ገርሞኝ የጸሃይ ሽንጥ ምነዋ ቀጠነብኝ ለወትሮው ከአድማስ እስከ አድማስ የሚዘረጋው ሽንጥዋ ወንዝ መሻገር አቃተ ው ብዬ ተገረምኩ። ተገርሜም አልቀረሁ አጠገቤ በመስኩ ላይ ካለ ፈረሰኛ አንዱን ጠየ ቅኩ። እንዲህም አለኝ ጸሃይ አልቀጠነች አልወፈረች ያው ነች። እዚያ ማዶ ጨለማ የሆ ነው ጊንጦች በጅብ ሞራ የሰሩት ጣራ ከልሎት ነው። በማለት መለሰልኝ።

እኔም አልገባኝም ብለው።ቋንቋችን ለየራስ ነው ብሎኝ ዞር አለ። እንደኔው ባማረ ነጫ ጭ ፈረስ ላይ ሆነው በሜዳው ላይ የሚጎማለሉ ብዙ ናቸው ። ሁሉም የሚጋልቡ ይመ ስሉኛል ግን አንዱም ሲርቅና ወደ ወንዙ ሲቀርብ አይታይም። አሁንም ከወንዝ ወዲያ ማዶ ጩኸት ይሰማል የሚንቦገቦገው እሳት ፈንጠርጠር ብሎ ለሁለት ክፍል በማለት ለ ሰከንድ ያህል ብርሃን ፈንጥቆ ደግሞ ቁል ቁል ወርዶ ክስም ሲል ታየኝ።

እንደኔው የእሳቱን መፈናጠር ያዩ ጉድ ጉድ ሲሉ ድንገት የቆምንበት ሜዳ ባለርስት አይቶ አርፋችሁ ሠራችሁን ሠሩ ከወንዝ ወዲያ ማዶ ያለው ጉዳይ የናተ አይደለም ብሎ ገሰጸን።ለካስ እንደኔ ፈረሰኛው ሁሉ በሜዳው ላይ በጥቋቁር ፈረስ ያሚንግማለለው የባለ እርስቱን እህል እየወቃ ነው። ሁሉም ወደስራው ተመለሰ። እኔም አሾልቄኘ ወደ ማዶ ሳይ ባለርስቱ የሜዳው ባለቤት ከወንዝ ወዲያ ላለው እሳት ማብረጃ ውሃ ይረጭ ጀመር። ውሃው ግን ጩኸቱን አባሰው እንጂ አልቀነሰውም። ቀጥሎም ከጠፋው እሳት ጭስ መሃል አንድ እንደ ፍየል ቀንዳም እንደ ጎሽ ማጅራታም ባለ 4 አይና ምስል በጅቦች መንጋ ታጅቦ ብቅ ብሎ ውሃ የረጨለትን የሜዳውን ባለቤት በምስጋና እጅ ነሳ። ከጎኑም ሌላ ጭስ መሃል እሱኑ የመሰለ አውሬ ብቅ ብሎ እጅ ነሳ። የጩኸቱ ድምጽ ግን አልበረደም።ብዬ ህልሜን ልቀጥል ስል ህልም ፈቺው አቋረጠኝ እስኪ ስሙት።

ህልም ፈቺው፥ ይህ ቅዠት እንጂ ህልም ነው ማለት ግድፈት ነው። አምሳል በባህሪ እንዳይወከል ባህሪው አንድ አምሳሉ ሺ ሆነ ባህሪም መጻዊውን ነገር እንዳያመላክት ምልክቱም ፍቺውን እንዳይሰጥ ሁሉም አንድነት ተቀየጡ። እሳት ባህሪው ነገር ነው። ውሃም ማብረጃው ነው። ውሃው እሳቱን ማጥፋቱ ሲሳይ እንዳይሆን መጻዊው ግዜ የመከራ ማብቂያነቱን እንዳያመላክት በውሃው መረጨት የተሰማው ጩኸት በርክቶ ባህሪ ውሃን አዛነፈው። ቢሆንም ባህሪ አይለወጥምና ማዶ ያየኸው እሳት ጸብ ነው። ውሃውም ጸብ አብራጅ ነው። ጩኸቱም ከወላፈን ወደረመጥ ሲሻገር ነው። አንተም ያለህበት ሜዳ ሰላማዊ ሰፈር ነው። ፈረሰኛው ሁሉ ልቡ ወደ ማዶ የተሰቀለው የደም ጥሪ ነው። የሜዳው ባለቤትም ባለጸጋና ተሰሚ ነው። ለወደደው ውሃ ለጠላውም እሳት ይሰጥ ዘንድ ይቻለዋል። ለባለብዙ ገጽ አስቀያሜ አውሬዎችም ውሃ መርጨቱ ቢመርጣቸው ነው። አውሬዎቹን ያጀቡት ጅቦችም ጸሃዩን የከለለው ሞራ ባለቤት መሆናቸው ነው። ቦሆዳቸው በሞራው ጣራ ስር ያደሩ ናቸው።በሜዳው የሚወቃው እህልም ሃብት ነው። ፈረሱም ምቾት ነው። አለመሸምጠጡም የስራ ውጥረት ነው። ቀጣይ ከሆነ እንጂ ይህ ህልምም አይደል።ቅዠት ነው።

አላሚው፥ በማለት ህልም ፈቺው ፍቺውን ሲያበቃ እኔም ህልሜን ቀጠልኩ። በሜዳው ላይ ያለነው ፈረሰኞች አንድም ሁለትም ሆነን ማንሾካሾክ ያዝን። ከወንዝ ወዲያ የምንሰማው ጩኸት እንዲቆምልን ተስማማን ወደ አሰሪያችንም ሄደን አቤት አልን። አሰሪያችንም ጩኸቱ የተለመደ ነው ። ምክንያቱም ረሃብ ነው በማለት ከወቃነው እህል በቁና ሰፍሮ ከወንዝ ወዲያ ማዶ በተነው እንደንስር አሞራ ጥፍርና ክንፍ ያላቸው ጅቦች በባለ ቀንዳሙ አውሬ ታጅበው እየተንሳፈፉ እህሉ መሬት ሳያርፍ ሰለቀጡት። አሁንም ጩኸቱ አልበረደም ይብሱኑ መባባሱ የሁሉንም ፈረሰኛ ቀልብ ሳበ። አንዳዱም ፈረሰኛ ስራውን ትቶ ውሃ ያበረደውን እሳት እንደገና ለማቀጣጠል ወደማዶ ፍም ይወረውር ጀመር። ፍሙ በሞራው ጣራ ላይ እያረፈ ይሸነቁረው ጀመር። በሽንቁሩም የጸሃይ ብርሃን እየገባ የአስጠሊታውን አውሬ መልክ ቀስ በቀስ ያጋልጠው ጀመር። ይህ መሆኑን ግን አሰሪያችን የመስኩ ባለቤት አልወደደውምና ፍም ወርዋሪዎችን ገሰጸ። ለአውሬውም አስቀያሚ መልክ መሸፈኛ ይሆነው ዘንድ ከሰው ደምና ቆዳ የተሰራ ብልኮ በሽልማት ላከለት አውሬውም ሽልማቱን ብሉኮ ቢለብስም አላማረበትም። ይብሱኑ ደምና ቆዳው እየከረፋ ቁም ስቅሉን አሳያው። አሁንም በሜዳው ላይ የሚገኙት ፈረሰኞች ፍም መወርወራቸውን ቀጠሉ። በተሸነቆረው የሞራጣራ የሚገባውን ብርሃን ያገኙትም መንቀሳቀስና አውሬውን መቆነጣጠጥ ተያያዙት። ጸሃይም ግረቷን ቀጠለች ሞራውም ሊቀልጥ ይሞቀሙቅ ጀመር። በዚህ መሃል በሜዳው ላይ ያለነው ፈረሰኞች የስራ ማቆሚያ ደውል ሲደወል ከእንቅልፌ ባነንኩ። እንግዲህ ያየሁት ይህንን ነው ቅዠትም ይሁን ህልምኘ ፈቺው ይንገረኝ።

ህልም ፈቺው፥ ቅዠትህ ፈር ይዞ ተህልም ሊዳበል ሲጠጋ መባነንህ አጉል ሆነ። መቋጫ የለውምና፥ ህልም ደግሞ ይተረጎማል እንጂ አይተነበይምና፥ መጻዊውን ተከታይ ነገር ሰናይ፥ ወይም እኩይ፥ ለማለት ከቶውንም አልተቻለም። ግና ጅምር እይታህ እንደ ማይጨበጠው አየር ተንገዋሎ የትም ካልቀረ መሬት ሊያርፍ ግድ ይለዋልና መሬትም ሲያርፍ ወይ ደረቱን ለአፈር ጀርባውን ለጣይ አልያም ጀርባውን ላፈር ደረቱን ለጣይ መስጠቱ ስለማይቀር። ሁለቱንም አወዳደቆች በፍቺ በፍቺቻው እንያቸው።

አሰሪያችሁ ጩኸቱን እንዲያበርድ ማለታችሁ የደም ጥሪ የአሻራችሁ ቅጂ አቤቱታ ነው። እሱም አለናተ አይሆንለትምና በቁና እህል በትኖ ጩኸቱን ሊያበርድ መሞከሩ ቢፈራችሁ ነው። የጩኸቱ ምክንያት ረሃብ ነው ማለቱም ንቀት ነው። የበተነው እህል የአውሬ ሲሳይ መሆኑ አስፈሪ ነው። ውሃ ያበረደውን እሳት ዳግም ለማቀጣጠል ፍም መወርወሩ ሲሳይ ነው እንዳልል የእሳት ባህሪ ቢያግደኝም ፍሙ በሸነቆረው ቀዳዳ ብርሃን መግባቱ ደግሞ ባህሪ እሳት ወደ ባህሪ ውሃ፥ ባህሪ ውሃ ደግሞ ወደ ባህሪ እሳት ዞሮ አምሳሉን ማመላከቱ ነውና ፍስሃ ነው። ብርህን ፈንጥቆ፥ ጸሃይ ሞቆ፥ በጅቦች ሞራና የወተት አንጀት የተሰራውን ጣራ ማሞቅሞቁ የዘመነ ሲሳይ መግቢያ ደፍ ነው። ፈረሰኝኣው ሁሉ አንድ ቋንቋ መናገሩም የሞራው ጣራ ፍጻሜ ነው። የአውሬው መልክ በብርሃኑ መጋለጡ ለአዳኞቹ ምቹ ይሆናልና ለጯሂው ወገን እሰየው ነው ። ባለመስኩ ሃብታም ለውሬው ብልኮ መሸለሙ የሞራውን መገፈፍ አለመውደዱ ነውና በሬ ካራጁ እንዲሉ ኑሮህ ከአጥፊህ መሆኑን ነው።ይህ እንግዲህ አልተቋጨምና ህልም ደግሞ ትርጉም እንጂ ትንቢት የለውምና ማጣፊያው ሁለት ሊሆን ግድ ሲል የቀኝ ማጣፊያውን ሲይዝ የሚያመላክተው መጻኢ ነገር ቅድሚያ እንይ።

በሜዳው ላይ ያለው ፈረሰኛ ፍሙን መወርወር ቀጥሎ ጣራው ስር ያለውም በጸሃይ ብርሃን ታግዞ አውሬውን ከሸነቆጠ ጸሃይም ግረቷን ጨምራ ሞራውን ካቀለጠችው ከወንዝ ወዲያ ማዶ ያለው ችግር እንደ ሞራው ይገፈፋል። ያኔ በሜዳው ላይ ያሉ ፈረሰኞች ሁሉ ወንዝ ተሻግረው ይከትማሉ። ያኔ ጥጋብ ደስታ ብልጽግናና ፍስሃ ወንዝ ተሻግራ ትሄዳለች ወንዙም እንደ ኩል ጠርቶ ሰራዊትን ሲያጠጣ አውሬው ደግሞ እንደሻማ ቀልጦ እስከመኖሩም ይረሳል። እሳትም ወደ ቋዋሚ ባህሪው ወደ ነገር ውሃም ወደ ማብረጃነታቸው ይመለሳሉ።ይህ እንግዲህ ህልምህኘ ማጣፊያው ቀኝ ሆኖ አወዳደቁም ደረቱን ለጸሃይ ጀርባውን ለአፈር ሲሰጥ ነው።

ያ ሳይሆን ቀርቶ በሜዳው ላይ ያለው ፈረሰኛ ፍም መወርወሩን ታክቶ፥ የሞቀሞቀው ሞራም በሜዳው ባለቤት ወሃ ተረጭቶ፥ መቅለጡ ቀርቶ፥ ከረጋና የተሸነቆረው የሞራ ጣራ ተደፍኖ ዳግም ጨለማ ከነገሰ፥ አውሬው ገበናውን መሸፈን ችሎ ዳግም ጅቦችን ካጎረሰ፥ መጻኢው ነገር እንደ እናት ሞት አስፈሪና አቃጣይ ነው።ይህ እንግዲህ ህልምህ ግራ ብሎት ደረቱን ላፈር ጀርባውን ለጸሃይ ሲሰጥ የሚያመላክተው እኩይ ተምሳል ነው። ለሁሉም መቋጫ እንዲኖረው መመኝት ብቻ ሳይሆን መቅዋጫው የቀኙን ማጣፊያ እንዲመርጥ ክፉ እልም እልም ብለህ ጠብቅ።ጉደኛ ነህና ዳግም ህልሜ ቀጠለ ብለህ እንደምትጠራኝ አውቃለሁ።አሁንስ እኔም ቀጣዩን ማወቅ ጓጉቻለሁና ህልምህ ሲቀጥል ጥራኝ። እስከዛው አደራ አለቃ አምባ ቆም ቢጠይቁህ ወደ ሰላ ድንጋይ ደብር አቅንቷል በላቸው። እዝህ ካንተጋ መዋዛቴን ካወቁ የኔ ነገረ ያበቃለታልና አደራ ሸበብ በል።እስከዛው ደህና ሰንብት።

አላሚው ብሎኝ ከፈቺው ተለያየን እናተንም እዚሁ ላይ ለያችሁ ህልሜ ከቀጠል እንገኛኛለን። እስከ ያ ደህና ሁኑልኝ ።