ወያኔ አቶ ልደቱን እንደጠቀመ እርግጠኛ ባንሆንም
አቶ ልደቱ ወያኔን መጥቀማቸው ግን ያፈጠጠ እውነት ነው!!
|
ወያኔ አቶ ልደቱን በጥቅም ገዛቸው! ወይም አቶ ልደቱ ከወያኔ ጠርቀም ያለ የገንዘብ ጥቅም አገኙ የሚለውንና በወሬ ደረጃ የሚንሸራሸሩትን ወቀሳዎች እውነተኝነት ማረጋገጥ ባንችልም። አቶ ልደቱ የብዙሃኑን የቅንጅት አመራር አካል ውሳኔ አልቀበልም በሚል የወሰዱት አቋምና! በተከታዩም ያደረጉት እንቅስቃሴ! እታገለዋለሁ የሚሉትን ወያኔን እድሜ ያረዘመ! መሆኑን ግን በርግጠኝነት እንናገራለን። አቶ ልደቱ
የፈጸሙት ተግባር ወያኔን እንደ ጠቀመ ! ትግሉንም በመጠኑም ቢሆን እንዳዳከመ ያምናሉ ወይስ አያምኑም የሚል ጥያቄ
ቢቀርብላቸው ምን እንደሚመልሱ አይታውቅም፡፤ ይሁን እንጂ መልሳቸው ምንም ይሁን ምንም በቋጠሮ ገጽ እምነት አቶ ልደቱ
አይደለም አሁን ገና ከጅምሩም የወሰዱት የብዙሃንን ውሳኔ ያለመቀበል ኢ-ዲሞክራሲያዊና አምባገነናዊ አቋም ወያኔን
እንደሚጠቅም አያውቁም ማለት የዋህነት ይመስለናል። የቋጠሮ ገጽ አቶ
ልደቱ አያሌው ላለፉት 14 አመታት ያደረጉትን እንቅስቃሴና በተለይ ወጣቱን ትውልድ ለትግል በማነሳሳት የተጫወቱትን ሚና
በእጅጉ ታደንቃለች! ለትግሉ እዚህ ደረጃ መድረስም ታላቅ አስተዋጾ ማድረጋቸውንም ታምናለች! ስለዚህም አቶ ልደቱ
ላለፉት በርካታ አመታት ያደረጉት እንቅስቃሴ ሁሉ በወያኔ ጉያ ሥር ተወሽቀው ለጥቅም ሲሉ የህዝብን ትግል የሰለሉበት
እንቅስቃሴ ነው የሚለውን አመለካከት የቋጠሮ ገጽ በፍጹም አትጋራም፡፤ እንደሚጠረጠረው አቶ ልደቱ የቅንጅቱን ብዙሃን
አመራር ውሳኔ ላለመቀበል ከወሰዱት አቋም ጀርባ ረብጣ ብር የተሸከሙ የወያኔ እጆች ቢገኙ እንኳን መደለያውም ሆነ
የድለላው ስምምነት የቅርብ ግዜ ተውኔት እንጂ የዘመናት እድሜ፡ያካበተ የውስጥ አርበኝነት ገድል አይመስለንም።ይህን
ስንል በጥቅም ተደልለው ከሆነ መቼም ተደለሉ መቼ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ጠፍቶን ሳይሆን! ያለፉት የትግል
እንቅስቃሴዎቻቸው ከዝህ በወገን ቆመው የታገሉ መሆናቸውን እንደምናምን ለመጠቆም ነው። አቶ ልደቱ ለምን
ለብዙሃኑ ውሳኔ አልተገዙም ሲባሉ! የሰጡት መልስ እኔም ያልኩት ብዙሃኑ ቀደም ሲል
የወሰነው ውሳኔ መሻር የለበትም ነው! የሚል ነበር። በጥቅም ተገዝተው ከሆነ ታሪክ ይፈርዳቸዋል በስልጣን እርከን ቅሬታ ተስምቷቸው የወሰዱት እርምጃ ከሆነም ከሕዝብ ጥቅም በበለጠ ለግል ስልጣን የሚታገሉ ሰው ናቸውና በመጻዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ህይወት ውስጥ ሊሳተፉ አይገባቸውም እንላለን። በመጨረሻም የህዝብ ትግል ያደራው በህዝብ መብት ዙሪያ እንጂ በግለሰብ ዙሪያ አይደለምና የአቶ ልደቱ ከትግሉ እንቅስቃሴ መገለል ራሳቸውን ብቻ የሚያገል እንደሆነ የቋጠሮ ገጽ እምነት ነው፡፤ አቶ ልደቱ ባደረጉት እንቅስቃሴ የተቸራቸውን ክብር ሁሉ በጥፋታቻው ተነጥቀዋል፡፤ ህዝባዊ ትግል ያሰራለትን አክብሮ ያሴረበትንም አስወግዶ የነገውን የትግል ሪትም ብቻ ተከትሎ ሁሌም ወደፊት የሚተም እንጂ ከታሪክና ከባለታሪክ ጋር ፍቅር እስከመቃብር ብሎ መቀመቅ የሚወርድ አይደለምና! የአቶ ልደቱንም ታሪክ የውሾን ነገር ያነሳ ብለን ትግሉን ማፋፋም አለብን! እንላለን። |