ያለ እዳው አልቃሽ
|
ይህ አሁን የማጫውታችሁ ታሪክ አስቂኝነቱ በቀልድ ጎራ ቢያሰልፈውምኘ እውነተኛ ገጠመኝ ነው። ገጠመኙን ያጫወተኝ ወዳጄ በቅርብ በሚያውቀ የሡፈሩ ሰው ላይ የደረሰ መሆኑን ገልጾልኛል። የወዳጄ ሡፈር ሰው እንዲህ ሆነላችሁ፥ ለእናቱ አንድ በመሆኑ ብዙውን ግዜ ከሠራ ውጭ የትም ቢሄድ እናቱ ደስ አይላቻውም። እሱም እናቱን ላለማስጨነቅ አብዛኛውን የእረፍት ግዜውን እቤት ውስጥ ነው የሚያሳልፈው።አንድ ቅዳሜ ቀን እንደተለመደው አልጋው ላይ ጋደም ብሎ የሬድዮ ፕሮግራም ሲያድምጥ ውሎ አመሻሽ ላይ እናቱም በሽተኛ ለመጠየቅ ወደ መንደር ጎራ ሊሉ ሲነሱ እሱም አየር ቢጤ ልቀበል ብሎ ይነሳል። " ከመሸ ደግሞ ወዴት ተነሳህ _ _ _? እባክህ ልጄ አርፈህ ቁጭ በል ቤትህ። የቅዳሜ ቀን ሰካራም ይጋጭሃል። እኔ በቁሜ ነው ደርሼ የምመጣው " በማለት እናቱኘ የተለመደውን ተቃውሞዋቸውን በማቅረብ ሊያስቀሩት ቢሞክሩም እግሬን ላፍታታ ብሎ ወጣ አለ። ከቤቱ ስለማይወጣና እንደሰፈሩ ወጣቶች ዘለል ዘለል ሲል ስለማይታይ በሡፈር ሰው በጣም ይወደዳል። እግዚአብሄር የባረከው የማይለው የለም። እናቱም ስለልጃው ጨዋነት ሳያነሱ የዋሉበት ቀን የለም። ከቤቱ ወጥቶ አውራ መንገዱን ጥግ ይዞ ነፋስ እየተቀበል የቆጡን የባጡን እያሰበ ጥቂት ደቂቃዎች እንደተጓዘ ከሰፈሩ ትንሽ ወጣ ብሎ ከሚገኘው የአካባቢው የመሸታ ክልል የሚሰማው ጆሮ የሚበጥሰው ሙዚቃ ካሃሳቡ አባኖት በመንገዱ ዳር መደዳውን ያሉትን ብና ቤቶች እየገረመመ አለፈ። ለመጠጥ ብዙ ግድ የለው። ዛሬ ግን የሆነ ነገር ጠጣ ጠጣ አሰኘው። ግን ፈራ። አንድ የሰፈር ሰው ካየው ስሙ ይጠፋል። ደግሞ መጠጣትም ፈለገ። የደሞዝ ሰሞን ስለነበር የገንዘቡ ጉዳይ አሳሳቢ አልነበረም። ግን ሰው ፈራ። የነበረው አምራጭ ሰው የሌለበት ቤት ፈልጎ ጓዳም ቢሆን ገብቶ መጠጣት ነበርና በአይኑ ጭር ያለ ቤት ሰያይማትር በጥግ ላይ አንድ ቤት ያያል። ወዲያው ሳያመነታ ግራ ቀኙን ተገላምጦ ዘው ብሎ ገብቶ ጥግ ፈልጎ ይቀመጥና የሚጠጣ ያዛል። ባዶ ቤት ታቅፋ የተቀመጠችው ኮማሪት እሱን ስታይ ፊቷ ሁሉ ጥርስ ሆኖ እየተፍለቀለቀች መጠጡን አቅርባለት እየተጎነጨ ጨዋታ ቢጤ ጀማመሩ። አንድ ሁለት 3 ሲል የሰው ፍራቻው ሁሉ ከራሱ ላይ ተገፎ ሄደ። "ደሞ ማን ምን አገባው በራሴ ገንዘብ እኔ ሕጻን ልጅ አይደለሁ "እያለ በራሱ ለራሱ ወኔ ሰጥቶ እግሩን አነባብሮ ተቀመጠ። በኋላማ ላንቺም አንጪ፥ ለኔም ቅጂ ሲል ሳይታወቀው ሰአት እላፊ ሆነ። በስካር መንፈስ ደፍሮ ለመሄድ ቢያስብም ሃይለኛ ዝናብ ያዘው። ጭራሽ 8 ከሌሊቱ መሆኑን ሲያውቅ ተስፋ ቆርጦ መጠጥ ደገመ። ኮማሪቷ እንደሌሎቹ ኮማሪቶች አይደለችም። ባለ ባል ነች ። በሌላ አንጋገር ያስቀመጣት አለ።ባሏ በጣም ስለሚቀና በሰፈር ሰላይ ያስጠብቃታል። እስዋም ይህንን ስለምታውቅ መጠጥ ከመሸጥ በስተቀር ብዙም ለወንድ ፊት አትሰጥም። ለዚህም ነው ቤቷ ጭር ያለው። አጅሬንም ቢሆን እንዲያድር አላደፋፈረቸውም። በኋላ ግን ስሜቷ ፈለገው። ጭራሹኑ እሷው ጋባዥ ሆና አረፈች። በቃ እዚሁ አድረህ ጠዋት ትሄዳለህ አለቺው።" ስለ ሰውየዋ ነግራው ስለነበር ፈራ። ግን አዲስ አበባ ውስጥ እንደሌለና ከሳምንት በፊት እንደማይመጣ ስትነግረው ተረጋቶ አንሶላ እየተጋፈፈ ለ3 ሰአት ያህልም ሳይተኛ። በሩን አንዳች ነገር ሲደበድበው ሁለቱም በድንጋጤ ባነኑ። "ማነው" አለች ። ወደ መብራቱ ማብሪያ እጅዋንኘ እየሰደደች ። "እኔነኝ" አሉ ከጎረቤቷ አንድዋ አሮጊት። ደነገጠች የባሏ አክስት ናቸው። ከወንድ ጋር ተኝታ ቢያይዋት አለቀላት። ቶሎ ብድግ ብላ ተነስ ተነስ ብላ ልታስነሳው አስባ ግን የት ትደብቀዋለች ቤቱ አንድ ክፍል። አግዳሚው መቀመጫ ላይም ብታስተኛው ማወቃቸው አይቀርም። ስለዚህ ያለው አማራጭ ወንድሜ ነው ከክፍለ ሃገር መጥቶ ነው ማለት እንደሆነ አስባ ለሱም ነግራ በሩን ከፈት ስታደርግ ያላሰበቺው ነገር ተከተለ። ጎረቤቶቿና እድርተኞቿ እያለቀሱ ገቡ።እናቷን ሊያረዷት ነው ለካ። ቤቱ በለቅሶ ድምጽ ቀውጢ ሆነ። አጅሬ ብርድልብሱን ለብሶ ጥግ ቆመ። ትንሽ ተለቃቅሰው ጋብ እንዳሉ ፍራሽ መሬት አውርደው ቤቱን ያዘገጃጁት የባሏ ዘመድ "ማነው እሱ ልጄ " እብለው እንደዋዛ ግን በቁጭት ይጠይቃሉ ። "ወንድሜ ነው ከክፍለ ሃገር ትናትና ገብቶ ነው" ብላ ፍርጥም ብላ ስትመልስ ቀልባቸው መለስ አለ። "አይ ልጄ እንግዳው አገሉ ነገር ላይ ደረስክ "። አሉ አንደኛዋ ሴት። አንደኛዋም ቀበል አድርገው። " አይ ሠጋ ስጋ እንዲህ ቀላል ነው መከራሽን ብቻሽን አትሁኝብሎ እኮ ነው እሱን ያመጣላት።" አሉ ። አጅሬ አይኑ ተቁለጨለጨ። በነጋና ከምኔው በሾለኩ ብሎ ሲይስብ ። ተነስ እንጂ ከወንበሩ ላይ ሂድ ፍራሹ ላይ ከእህትህ ጋር ተቀመጥ ብለው ጭራሽ አመቻችተው አስቀመጡት። ረፈድፈ ሲልም ቁርስ ከተበላ በኋላ አንደኛዋ ሴት ምላጭና ሳሙና ይዘው መጥተው የኮማሪቷን ጸጉር ላጭተው ሲጨርሱ ሌላኛዋ የሰፈር ሴት "ምነው እሱንም በነካ እጅሽ አትላጭውም ለሱ እንደገና ልትመጭ ነው።" ይላሉ። አጅሬ ደነገጠ ኮማሪቷም "እሱ እንኳን ይቅርበት ገጠር ስለሚሰራ ብርዱን አይችለውም" ብላ ልታስጥለው ስትሞክር። " ምነው፥ ምነው፥ እናትህ የዘጠኝ ወር ቤትህ ከምስጥ ተዳላ አፈር ተጭኗት አንተ ባርኔጣ የሚከልለውን ብርድ ፈርተህ ጸጉርህን አጎፍረህ ለአንድ ቀንም ላትሆናት ነው ምነው ምነው ነውር አይደለም እንዴ" በማለት ከግራ ከቀኝ ሲያዋክብት ለመናገርም ፋታ ሳያገኝ ጸግሩ በሳሙና ርሶ የገሸለጥ ጀመር። ኘአጅሬ ጸጉሩንም ተላጭቶ ከገባው ለቅሶ ደራሽ ጋር እየዬውን ተያያዛው። ካሁን አሁን የማውቀው ሰው ይገባና ጉድ እሆናለሁ ብሎ ሲጨነቅ። ጭራሽ የናቱን ድምጽ ከውጭ ሰምቶ አረፈው ።ወዲያውኑ እራሴን አመመኝ ብሎ ጥቅልል። አለ። እናቱ ገብተው ትንሽ ቁጭ ካሉ በኋላ ከመሸ ወጥቶ ስለጠፋው ልጃቸው ጭንቀታቸውን ለለቀስተኛው ሲያዋዩ አጅሬ ብርድ ልብሱ ውስጥ ሆኖ ይንቀጠቀጥ ጀመር። እናቱ እንደማልቀስም እየቃጣቸው ወይኔ ልጄ እያሉ ሲጨነቁ ለቀስተኛውም ሲያጽናኛቸው ቆይተው ሊወጡ ሲሉ የልጃቸውን ጃኬት ወንበር ላይ ተንጠልጥሎ ያዩታል። ጃኬቱ ኪሱ ላይ ቀለም ፈሶበት በበረኪና አስለቅቃለሁ ብለው ያነጡት እሳቸው ስልሆኑ የልጃቸው መሆኑን ምንም አልተጠራጠሩም። ይብስ ብለው ጎንበስ ሲሉ ጫማውም ቁጭ ብለዋል። የዚህን ግዜ "ልጄን ገለው ገፈውት ይህው ልብሱ ይኸው ጫማው ያገር _ _ _ ያለህ የህግ ያለህ ማነው የልጄን ገዳይ ፍረዱኝ ይሄው ማስረጃው" እያሉ ጃኬቱን ይዘው ሲጭሁ አጅሬ ከዚህ በላይ ሊቆጣጠረው ስላልቻለ ብርድልብሱን እንደተከናነበ ሰውን በረጋግዶ እግሬ አውጭኝ አለ። የሱን መሮጥ ያዩ ጎረቤቶችና ቤትውስጥ የነበሩት አስተዛዛኞችኘ ወንጀሉ ስለታወቀበት የሚሮጥ መስሏቸው ያዘው ያዘው እያሉ ተከተሉት እሱም ዞር ሳይል ሮጦ ወደ አንዱ ጥግ ወተፍ ብሎ አመለጠ። ኘኘ ለቀስቶኞቹ ሁሉ ኮማሪቷን አይንሽ ላፈር ብለው አብጠለጠሏት። ኮማሪቷም እውነትም ነፍሰ ገዳይ መስሏት በሁኔታው ተደናገጠች። ወዲያው ፖሊስ መጥቶ ለጥያቄ ወደ ጣቢያ ሲወስዳት ተደብቆ የሚያየው አጅሬ አዘነላት ቀስ ብሎ አንድ ሊስትሮ ይልክና ከፖሊሶቹ ኋላ ኋላ እዬዬቸውን እያስነኩ የሚሄዱትን እናቱን ልጅዎት እቤት ነው ብሎ እንዲነግራቸው ያደርጋል ፖሊሶችም ኮማሪዋን ጣቢያ አድርሰው ወደ አጅሬ ቤት ሲሄዱ አጅሬ አልጋ ውስጥ ተጋድሞ ተገኘ። ኮማሪቷም ተለቃ ወደ ሃዘኗ ተመለሰች። አጅሬ እናቱን ማታለል ቢችልም የፖሊሶቹን ጥያቄ ማምለጥ ስላልቻለ እውነቱን ተናግሯል። እናቱ ግን ምንም ነገር ስይገለጽላቸው በልጃቸው መገኘት ብቻ በደስታ ሰክረው በቀጥታ ያመሩት ምስጋናቸውን ለማቅረብ ውደ ቤቴክርስቲያ ነበር። አያድርስ ነው እንጂ ሌላማ ምን _ _ _
|
