Poems                                                 ግጥም

  Back Home      Articles          Poems           News              Jokes               Email Us

        THIS WEBSITE IS CURRENTLY BLOCKED IN ETHIOPIA


ወግድ አለ ታዬ !
 


 

ወግድ አለ ታዬ ፥ ታዬ አባ አስደንጋጩ፥

በጥቁር ሰሌዳ ጠመኔ አቁነጥናጩ

ወግድ፥ አለ ወግድ፥ ሌላ ፈሪ ብላ

ሀሞተ ቢስ ፈልግ ግልድሙ የላላ

እኛማ ወንድነን ሱሪ ነው ልብሳችን፥

ምላስ ነፍሶ አይገልበው፤ ጥብቅ ነው ትጥቃችን፥

ወግድ ማስፈራራት፥ ወግድ፥ ዛቻ ወግድ ፥

ተንበርካኪ የለም በፍርሃት የሚርድ፥

እጀ ሙቅ፤ እግረ ሙቅ፤ ጌጡ ነው ለጀግና፥

እስር ጫጉላ ቤቱ ሞቱም ሙሽርና

እያለ እያገሳ፥ ያቆፍጣና አንበሳ

ወደ እናቱ ሊበር፤ ከኢሮፕ ሲነሳ

የአሳሞች ችሎት ክስ እንደሚጠብቀው

ከቶ መቸ ጠፍቶት ንቆ እንጂ ያለፈው

በተኩላ ተከሶ አሳማ መስክሮ አሳማ እንደሚፈርድ

እጀ ሙቅ አጥልቆ ጉሮኖ እንደሚወርድ

ለሱ መቼ ጠፍቶት ..........

ያ ወንድነቱ እንጂ ሽሽት አስጠልቶት

ዘብጥያ ፥ ከርቸሌ ፥ ጉሮኖ፥ መከርቸም

ቶርቹ ወፌ ላላ ሌላም ደግሞ ሌላም _ _ _

መቼ አርዶት ልቡን እንደወጣ ቀረ

መጣ እንጂ አባ ደፋር መጣ እየበረረ፥

የማሪያም መንገዱን አሳሪው የሰጠውን

መጥተህ አትሞግተን በዛው ጥፋ አይነቱን

መቼ ተቀብሎ መቼ ከቁብ ቆጥሮ

መጣ እንጂ አባ ደፋር መጣ እንጂ አምርሮ

ወግድ ፈሪ ብላ ግልድማሙን አማል

የኛማ ሱሪነው አይወልቅ አይዋልል

እያለ ገስግሶ _ _ _

የሃቅ ካባ ለብሶ

ከርቸሌ ሲገባ ከጢያራ ወርዶ

ሥም ከሌለው ምቾት ቱሃን ተባይ ወዶ

አለም ሆ አለ ለሱ ለዚህ ላባ ደፋር

ለቀለም አባቱ ለጠመኔው ሹፌር

ደሞ እኮ የሚገርመው ....

ያችኑ ጉሮኖ በዛችብህ ብለው

ተዳበሉት አሉ ከዘብጥያ ወርደው

ሩህሩህ ነውና ወትሮም ጀግና አንጀቱ

አዝንዎ አዳበለ እንጂ መች ጠቆረ ፊቱ

በዛችው ጉሮኖ ሁሉም ተጨራምቶ

ሁሉም ተኮራምቶ

ዋል አደር እያሉ እየተላመዱ ቃል ሲለዋወጡ

እሱም ጣል ሲያደርግ እነሱም ሲያምጡ

ወዳጅነት ሲጠብቅ ቀስ በቀስ ሲያቃቸው

ያላዋቂ አጥፊ ሆነው ቢያገኛቸው

ይቅር ለግዜር ብሎ ከጸጸት ፈታቸው

ግና ሞረዳቸው አስተካከላቸው

በአስተሳሰቡ አምሳል ዳግም እንደገና

ለውሶ አቡኩቶ ጠፍጥፎ ሰራቸው

ደርሶ ጢቅ አድራጊው ምራቅ ተፊ አፋቸው

ምራቅ ዋጥ ማድረግን መምህር አስተማረው

ያን የጎሳ ካባ ያጠለቁትን

ያን የዘር ዛር ጣኦት ያመለኩትን

መምሬ ገዝቶ ባርኮ አስወልቋቸው

ከኛው ጋር በአንድነት አጊጡ አላቸው።

ይህ አዋቂ መምህር ....

ዛሬ ነጻ ወጥቶ ሲለያቸው ድንገት

እንባ እየተራጩ ነው አሉ የሸኙት

ያ ጀግና በቁስሉ ፍቅር አሳያቸው

የጠፉትን በጎች ፈልጎ አገኛቸው

ታስሮስ መች ታሰረ ታዬ አባ ደፋሩ

ያ ሰሌዳ ቧጣጭ ጠመኔ ሹፌሩ።_

ወግድ አለ ታዬ ሌላ ብላ ሌላ

ሃሞተ ቢስ ፈልግ ግልድሙ የላላ

የኛማ ሱሪ ነው አይወልቅ አይገለብ

ዛቻ ቢያዥጎደጉድ ምላስ ቢርገበገብ

ወግድ አለ መምህር ታዬ አባ አስደንጋጩ

በጥቁር ሰሌዳ ጠመኔ አቁነጥናጩ።

 

ማስታወሻይህ ግጥም በተቀነባበረ የሃሰት ውንጀላና ፍርድ በወያኔ እስር ቤት ለ6 ኣመታት ሲማቅቁ ኖረው በሕዝብ ጩሀትና አቤቱታ በቅርቡ ነጻ ለወጡት ለኢትዮጵያ የክፉ ቀን ልጅ ለጀግናው መምህር ዶክተር ታዬ ወልደሰማያት የክብራቸው መታሰቢያ እንዲሆን በቋጠሮ ገጽ ዝግጅት ክፍል የተበረከተ ሲሆን ዶክተር ታዬ በነጻ ይፈቱ ዘንድ በቋጠሮ ገጽ ላይ በነበረው የአቤቱታ ማሰባሰቢያ ቅጽ ላይ ድጋፍችሁን ላሰፈራችሁ አንባቢያን ደግሞ ይህች ግጥም የምስጋናችን መግለጫ ትሁንልን እንላለን።

የቋጠሮ ገጽ ዝግጅት ክፍል ሳ . አ