Poems                                                 ግጥም

  Back Home      Articles          Poems           News              Jokes               Email Us

        THIS WEBSITE IS CURRENTLY BLOCKED IN ETHIOPIA

             
ማን ነበረ ጳውሎስ ...?

                                       
                                              
                                   

እስኪ መለስ ብለን ታሪኩን እንዳስ
እረ ለመሆኑ ማን ነበረ ጳውሎስ ...?

ያለ ረዳት ወገን ብቻውን ተፈጥሮ
ከሕይወት ግብ ግብ ብቻውን ጀምሮ
እንቁላል ቀቅሎ ቸርችሮ ለማደር
የኑሮን አቀበት ሊገፋ ሲጣጣር
አልሳካ ቢለው ገዢ አጥቶ እንቁላሉ
ስለታሙ አይምሮው ያ የለጋ ብስሉ
መላውን ፍለጋ አውርዶ አውጥቶ
በፈጠራው ክህለት አዲስ ዘዴ አግኝቶ
ቅቅሉን እንቁላል ቀለማት ቀብቶ
ብቅ ሲል ገበያ ዳግም ሊቸረችር
በጳውሎስ ብልሀት አገር ጉድ ይል ጀመር
ገበያውም ደራ ጳውሎስ ስሙም ናኘ
አንድ የልጅ አዋቂ ከደደር ተገኘ
እንዲህ እንዲህ ነበር የጋሽ ጳውሎስ ህይወት
ደጋፊ አልባ ሆኖ ...ኑሮውን የገፋት

ገና በለጋ ዕድሜው ዕውቀትን ቢሻትም
አንድ አይነድ ሆነና አልተሳካለትም
ሸቅሎ መማሩ አልቻልህ ቢለው
4 በላይ ሳይዘልቅ ተገደደ ተወው
ግና እሱ ነውና ጳውሎስ አባ መቻል
እራሱን አስተምሮ ከምሁሩ ልቋል
......እንዲህ እንዲህ ብሎ
በልጅነት እድሜው የማይቻል ችሎ
እራሱን አኑሮ ...
እራሱን አስተምሮ ...
ብቅ አለ ለአንባቢ ጳውሎስ አባ መቻል
በዘመን ላይ ኩሎ የብዕሩን ጸዳል
ታሪክን አጥንቶ ለወገን ዘከረ
ያልተማረው ምሁር ትውልድ አስተማረ

መች ማስተማር ብቻ የጳውሎስ ገድሉ
ክቡር ድንቅ ዜጋ ተወዳጅ ...መባሉ

በአምባሰል ቦረና ደሴ ድፍን ወሎ
ወገን በርሀብ ሲቃ ቆሽት አንጀቱ ቆስሎ
እዬየው ሲደመጥ ድረሱልኝ ብሎ
ጳውሎስ አባ መቻል እንባውን እረጭቶ
..............ህዝብን እንባ አራጭቶ
ለወገን ደራሹን ወገን አነሳስቶ
የለት ደራሽ ጉርሱን ሰንቆ አክቶ
ወገን አፈር ሳይቀምስ ጠኔ ሳይጨርሰው
አባ መቻል ደርሶ ህይወቱን ታደገው
ሺህ ህይወት አትርፎ ሺህ ህይወት አኖረ
ጳውሎስ በርሀብ ላይ ...ድልን አበሰረ

መቼ ይሄ ብቻ የጳውሎስ ገድሉ
ክቡር ድንቅ ዜጋ ተወዳጅ መባሉ

የራቀን አቃርቦ የተጣላ አስታርቆ
የተሳሳተውን በምክር አርቆ
ስርአት አስተምሮ
ባህልን ዘክሮ
ሺህ ሆኖ የኖረ ማነው እንደ ጳውሎስ ...?
ጋዜጠኛ ሆኖ ዜናውን ሲያቃምስ ...
በደራሲነቱም ጥፎ የተወ ቅርስ
ሰባዊነት ታጥቆ ለወገን የሚደርስ
የተጣላ አስታርቆ ፍቅር የሚያነግስ
የጠፋ የሚያገኝ ፈልጎ እንደ ፖሊስ
ሺህ ሆኖ የኖረ ማነው እንደ ጳውሎስ ...?

እናም ወገኖቼ ....!
ጳውሎስ አባ መቻል የጥበብ አክሊሉ
ክቡር ድንቅ ዜጋ ትወዳጅ መባሉ
በንባብ በቀልዱ በመጣጥፍ ገድሉ
ብቻ አይደለምና ጳውሎስ መዘከሩ
አንድ ሆኖ ተፈጥሮ ሺ ሆኖ መኖሩ
ለትውልድ ይተረክ ሁለገብ ግብሩ
የአባ መቻል ሥራ ይለፈፍ ይታወቅ
የአንድ ብዙነቱ ይታወስ ይደነቅ :;

ሳ/አ