Poems                                                 ግጥም

  Back Home      Articles          Poems           News              Jokes               Email Us

        THIS WEBSITE IS CURRENTLY BLOCKED IN ETHIOPIA


አበጀን ! አበጀን !
 


 

በሃምሌ 19፥ በዕለት ቅዳሜ፥ በሰንበት ዋዜማ፥

የኢትዮጵያ ጎበዛዝት ፥ ቃለ ህብረት ፥ሲሰማ

አሜን አሜን አለ፥ ተመስገን ተመስገን፤

እድሜ ፈቃድ ቸርዎት፥ በቁም ያለው ወገን።

ለእድሜም እድሜ ይስጠው ለዚህ ላበቃነ

ግፍ ጣሩን አስችሎ ይህን _ _ _ _ ላሳየነ

ለሰጪ እድሜ ይስጠው አለ አመሰገነ        

በቁም ያለው ወገን በእውኑ እየባነነ

ከቤተ መቃብር ...

ከርምርሙ አፈር ...

የአበው ጀግኖች ሆታም ደስታቸው ተሰማ

በሃምሌ 19 በዕለተ ቅዳሜ በሰንበት ዋዜማ

 

አበጃችሁ አሉ አበው ጀግኖቻችን

እውነትም እውነትም እውነትም አበጀን

የማይበጅ ስናበጅ እስካሁንም ባጀን

የነፍስ ወከፍ ፍልሚያ

የነጠላ ግጥሚያ

እንዳይበጅ እያወቅን

የሊቅ አጥፊ ሆነን

ድፍን፥ 12፥ አመታት ቆጠርን

ለሡራበትማ እድሜ ጸጋ ነበር

ሺ አመትስ፥ ቢቆጠር ...?

እንኳን ለሡራበት ቀምቶም ላደረ

የደም ልውስ አፈር ሸቅጦ ለኖረ

ለዴዶቹም ሳይቀር የእድሜ ጸጋ ተርፎ

አምነሽንሷቸዋል ያገር ቅርስ ገፎ

ግና ላልሰራበት ለእንደኔና እንዳተው

ውል አይረሳው እድሜ ግፉን አስቆጠረው

 

እንዲያ ነው እንዲያ ነው

እድሜ ያላስተማረው

ግፍ ነው አስተማሪው

ዋናው መማሩ ነው

እንዲያ ነው እንዲያነው

ተግፍ ተፍልቅቆ ችግር ያዳወረው

የዛሬውም ህብረት የበደል ፈትል ነው

በጥበብ አስጊጠን ቋጭተን ከለበስነው

ለኔም ላንተም ለሱም መጋጊያጫችን ነው።

 

አበጀን አበጀን እውነትም አበጀን

የማይበጅ ስናበጅ እስካሁንም ባጀን

እናም ወገኖቼ

ቃል ኪዳን መግባቱ

ሕብረት መገኘቱ

ማህበር መመስረቱ

እሰየው ቢያኝም አበጀን ቢያሰኝም

የወያኔም ጓዳ ረበሽበሽ ቢልም

አሃዱ ነው እንጂ አሜን አልተባለም

ወደ ትግሉ ጎራ ገና አልተተመመም

 

ይልቅስ መበርታት ማሰብ ያለብን

የማሌሊቱ ቄስ ተብታቢው ካህን

አፍዝ አደንግዙ በቋንቋ የመተተው

በየክልሉ አፈር ማምሶ የቀበረው

ድንገት ሲገኝበት መፍትሄ ማርከሻው

አርፎ አይተኛምና ለሌላው ትብታብ

ምንስ ያስብ ይሆን...? ብለን እናስብ

ልዩነታችንን በአንድነት ውስጥ ይዘን

ለዘር ዛሩ ጋኔን ቀዳዳ ካልሰጠን

አፈሙዝም ቢያዞር ድሉ የሕዝብ ነው

ወያኔ መንምኗል ሲሶው ነው የቀረው

ኪሲሶውም ሲሶው ከርሳም ነው ሆድ አደር

ይታዘዛል እንጂ አይመክር አይዘከር

ይባርክልን እንጂ ማበራችንን

ከእንግዲህ ወያኔ ስጋትም አይሆን

 

ተዋህዶን ነቅፎ አናንቆ አርክሶ

ተሃድሶን ሲሰብክ አዳንቆ አወድሶ

ቀናዊ ነውና ትግራይ ለሃይማኖቱ

በማሌሊቱ ቄስ ቆሽቱ አሯል አንጀቱ።

እንግዲህ ካህኑ ምን ወገን ቀረው

ከአንድ ዳዊት በቀር ቤቱም ባዶነው

እነኛ ሆዳሞች የሚቀልባቸው

ለሱም ትዝ አይሉት እኔም አልቆጥራቸው

 

አበጀን አበጀን እውነትም አበጀን

የማይበጅ ስናበጅ እስካሁንም ባጀን

እናም ወገኖቼ

ቃል ኪዳን መግባቱ

ሕብረት መገኘቱ

ማህበር መመስረቱ

እሰየው ቢያሰኝም አበጀን ቢያሰኝም

የወያኔም ጓዳ ረበሽበሽ ቢልም

አሃዱ ነው እንጂ አሜን አልተባለም

ወደ ትግሉ ጎራ ገና አልተተመመም

አድርዎ ቃርያ እንዳይሆን ማስጋቱም አይቀርም

እንዲያውም እንዲያውም ከወያኔ በፊት

ለዘብተኛውን ነው አጥብቆ መዋጋት

በተለይ በተለይ ባህር ማዶ ያለን

ለዘብተኝነቱ እኛን ነው ያጠቃን

በግፍ እቶን እሳት የሚንገበገበው

ካብራኩ ተገኝተን ከጅግሩ የራቅ ነው

ምስኪኑ ወገናችን .....

እሱ .... ዛሬ ሰላም ሲያጣ እኛ ሰላም ያገኘነው

ህሊናችን ሰላም ካለው

እሱ ጉርስ አጥቶ ሲያቃትት እኛ ብፌ ምናነሳ

ሆድ መቼም ህሊና የለው !

እውን የአርባ ቀኑ ስፍር

የእድል ቀመር

ለኛ ሞልቶ ለሱ ደግሞ ጎድሎበት ነው ?

ወይስ ለኛው ፍካት ሲል ነዶ ነው ?

ለኛ ብራን ሲል ቀልጦ ነው ..?

እናም እዳ አለብን ..!

የሀገርቤቱ ወገናችን እዳ አለብን ..!

በዶላር አይመነዘር

በመሃለቅ አይፈር

የደም እዳ ነው እዳችን

በደም መክፈል ነበረብን

እሱም ይቅር _ _ _ _

ቁስሉ እንዴት አይሰማንም

ስጋችን እንዴት አይስበንም

እና ስሙ ....

ፖለቲካ አንወድም ባዮች እንስማማ ስሙኝ አንዴ

ፖለቲካን አትውደዱ ምናባቱ ይሄ ውርዴ

አፈር ይብላ ድብን ይበል እኔም አብሬ ልጥላላችሁ

በደረሰበት አትድረሱ ሳትወዱትማ ምንተዳችሁ ?

ግን ሃገር መወደዱን አትርሱ

ለሕዝብ ማሰብን አስታውሱ

ሕዝብ ሲበደልም አልቅሱ

ይሄ ፖለቲከኛም ከዚህ ሌላ አጀንዳ ካለው

እናተ ብቻ ሳትሆኑ እኔም ጠልቼዋለሁ

 

አበጀን አበጀን እውነትም አበጀን

የማይበጅ ስናበጅ እስካሁንም ባጀን

እና ወገኖቼ .....

ለሃገር ማሰብ መብከንከን

ለሕዝብ መጨነቅ መባዘን

በደም እንጂ በስልጠና

ከቶውንም አይመጣምና

የዜግነት ግዴታ ነው

ለዘብተኝነት ካልሻረው።

ሰላምም የምትገኘው _ _ _ _

አገውም ከንባታው ኦሮሞው አደሬ

ጉራጌው አማራ ወላይታ ትግሬ

ኮንሶ አዳይታ ወይጦና ጋንቤላ

ሱማሌው አፋሩ ጊሚራው ጉዴላ

በአንድ ኢትዮጵያ አማክሎ

ለአንድ ኢትዮጵያ ብሎ

ባንድ ሲተም ነው።

የግፍ ውልድ ነውና ትግሉ

የማያዳግም ይሆናል ድሉ።

በሃምሌ 19፥ በዕለት ቅዳሜ፥ በሰንበት ዋዜማ፥

የኢትዮጵያ ጎበዛዝት ፥ ቃለ ህብረት ፥ ሲሰማ

አሜን አሜን አለ፥ ተመስገን ተመስገን፤

እድሜ ፈቃድ ቸሮት፥ በቁም ያለው ወገን።

ከቤተ መቃብር

ከርምርሙ አፈር

የአበው ጀግኖች ሆታም ደስታቸው ተሰማ

በሃምሌ 19 በዕለተ ቅዳሜ በሰንበት ዋዜማ

አበጃችሁ አሉ አበው ጀግኖቻችን

እውነትም እውነትም እውነትም አበጀን

የማይበጅ ስናበጅ እስካሁንም ባጀን።