News                                                      Archive

Back Home               Articles              Poems           News              Jokes               Email Us

የሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የካይሮው እንግድነት ሚስጥሩ ምን ይሆን

የሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የካይሮው እንግድነት ሚስጥሩ ምን ይሆን?

 

ከሁለት ውራት በፊት የአባይ ተፋሰስ ሃገሮች በአባይ ወንዝ ተጠቃሚ ለመሆን ቁርጠኛ አቋም መውሰዳቸውና ይህም ዜና ካይሮን ሲያርበደብድ እንደ ነበር ተደምጥዋል፡፤  ነገሩ ያስደነገጣት ካይሮ አባይን የነካ በአይኔ መጣ አይነት በሃይል ለማስፈራራትም ሞክራለች፡፤ ይህንኑ የግብጽን ማስፈራሪያ ተመርኩዘው  ጠ/ሚኒስትር መለስ በሰጡት ምላሽ፡፤

አባይን ለመጠቀም የሚያግደን ድህነታችን ብቻ ነው፡፤ ግብጽ አባይን እንዳንጠቀም ለመገደብ በመጀመሪያ ኢትዮጵያን በሓይል መያዝ ይኖርባታል!ይህ ደግሞ በታሪክ ተፈጽሞ ያማያውቅ ነው!!! በማለት የካይሮን ፉከራ የሚያናንቅና የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያደምቅ  ምላሽ በመስጠታቸው ይታወሳል። ይህ የጠ/ሚ ያልተለመደ የሃገር ተቆርቋሪነት ስሜት በተለይ ኢትዮጵያዊውን ሁሉ አስገርሞ አልፏል፡፤ እኝህ ሰው በጤናቸው ነው ? ያንን  የትምክህተኞች ታሪክ የሚል የስላቅ ስያሜ የሰጡትንና እንደ እናት ገዳይ የሚጠሉትን የጀግንነት ታሪክ ዛሬ ካየሮ ላይ የመዘዙት ምን አስበው ነው? ያላለ አልነበርም።

ገሚሱ በቀጲጸ ተስፋ ሲደመም ገሚሱ ደግሞ  ወያኔ እንደ እባብ ቆዳውን እየለዋወጠ የተፋውን ቃል መልሶ እየዋጠ የሚኖር ስለመሆኑ  ከ 13 አመት የምዝበራና የማጭበርበር ታሪኩን ዋቢ በመጥቀስ ከራሳቸው ከጠ/ሚ አባባል በመዋስ ትኩረታችን በፉከራው ላይ ሳይሆን  ከፉከራው ጀርባ ባለው  ደባ ላይ ነው !! ሲል ሰንብቷል;

ይህ በእንዲህ ቆይቶ ከጥቂት ቀናት በፊት ጠ/ሚንስትሩ በምድረ ግብጽ  ጉብኝት ማድረጋቸው ደግሞ የሰሞኑ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል፡፤የጠ/ሚንስትሩ ጉብኝት የዘገቡት የዜና አውታሮች ሁለቱ መሪዎች በአባይ ወንዝ   አጠቃቀምና በአፍሪካ  ልማት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ከመዘገባቸው በስተቀር የውይይቱ እሴት በውል አለመታወቁ ጉዳዩን የበለጠ አነጋጋሪ አድርጎታል፡፤ አብረዋቸው የተጓዙት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መስፍን ከካይሮ አቻቸው ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የስምምነት ውል መፈራረማቸውም ተዘገቧል፡፤

ከሁለት ወር በፊት በሁለቱ ሃገሮች መካከል የነበረው አለመግባባት ምንጩ  ሁለቱም ወገኖች ለልማት ያላቸው ፍላጎት ይመስል ስለነበር  ግራውንም ቀኙንም  የሚያስማማ ውል ለምቅረጽና ውዝግቡን ለማብረድ ረዘም ያለ ግዜ ሳይወስድ እንደማይቀር ቢገመትም በሚያስገርም ፍጥነት ጎራዴ ወደ አፎቱ ገብቶ ፍጹም በሆነ ፈገግታ የታጀበ ውይይትና መስተንግዶ መከናወኑ ኢትዮጵያዊውን ክፍል አስገርሟል፡፤

 በእንዲህ አይነት ፍጥነት የሚገኝ ስምምነት ደግሞ የግድ አንዱ ወገን የይገባኛሉን ጥያቄ ሲያነሳ ወይም ለይገባኛል ጥያቄው አማራጭ ምላሽ ለመቀበል ሲፈቅድ ብቻ ነው፡፤ ግብጽ ደግሞ በአባይ ላይ ያላትን የይገባኛል ጥያቄ በምንም ነገር የምትለውጥ አለመሆኗን ስናስተውል፡፤ አማራጭ ምላሽ የሚለው ነገር ወደኛው ሲያነጣጥር ይታያል፡፤ ያም ሆነ ይህ እስካሁን ድረስ  የሰላሙና የስምምነቱ ሚስጥር ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ በግልጽ የሚመልስ ከወያኔም ሆነ ከሙባረክ መንግስት የተሰጠ መግለጫ  የለም። ይህ ደግሞ ጉዳዩን ውስብስብ አድርጎታል፡፤

ግብጽ በአባይ ወንዝ ተፋሰስ ሃገሮች በየግዜው የሚነሳውን የይገባኛል ጥያቄ ባለስልጣናቱን በገንዘብ እየገዛች እንዴት አድርጋ አፍ ስታዘጋ እንደኖርች ብዙዎች በብዙ መድረክ ገልጸውታልና አልደግመውም፡፤   ኢትዮጵያዊው ዜጋ የጠ/ሚንስትሩ ፉከራ በዚህ ፍጥነት በሞቀ መስተንግዶ መለወጡ ያሰጋውም  ካይሮ የተፋሰስ ሃገሮችን ባለስልጣናት ስትደልል የመኖር ልምዷን ስለሚያውቅ እንጂ ሰላምና የጋራ ልማት ጠልቶ አይደለም፡፤ይህ የካይሮ የቆየ ልምድ አሁንም ....የማይሰራበት ምንም ምክንያት የለም! ከወያኔ ባህሪ አንጻር ሲመዘን ደግሞ ግምቱ እውነትነቱ ይደምቃልና በጠ/ሚ ፉከራ ማግስት ..... ትኩረታችን በፉከራው ላይ ሳይሆን  ከፉከራው ጀርባ ባለው  ደባ ላይ ነው ! ያለው ወገን  አስተውሎቱ ሚዛን የደፋ ይመስላል!!! ታሸም ተበጠበጠም የኢትዮጵያ ህዝብ  ለእንቆቅልሹ ምላሽ ይሻል፡፤

ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ ለመዘርጋት ያሰበቺውን ከ 600 ቢልዮን ዶላር በላይ የመደበችለትን ፕሮጀክት የሰረዘቺው የተፋሰሱ ሃገሮች ጉርምርምታ ስላሳሰባት ሳይሆን እንደማይቀር ከጉዳዩ ጋር ቅርርብ ያላቸው አካሎች ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፤ በተለይ 85% የአባይን ውሃ የሚመነጭባትን ኢትዮጵያን ሳታረጋጋ ይህን ያህል ወጪ የተመደበለትን ፕሮጀክት መጀመር ውጤቱ እንደማያምር በመረዳት ካይሮ ማስፈራራቱንና ዛቻውን ተወት አድርጋ ኢትዮጵያን ለማግባባት እንደ አማራጭ የተጠቀመችበት መንገድ ምንም ይሁን ምን ሳይሰራላት እንዳልቀረ ከጠ/ሚኒስትር ፈገግታ መገመት ይቻላል።


ምንድነው ሚስጥሩ?

እውን የጋራ ልማት ?????

ወይስ

ያአባይን ነገር ያነሳ! ......ይሁን!
ውል ?

በዚሁ ሰሞን  ሙባረክ ኢሳያስ አፈወርቂን ማነጋገራቸው ደግሞ ሌላው ካይሮ ልትጫወተው የፈለገችውን ሚና ግልጽነት ያወሳሰበ ጉዳይ ነው፡፤ ጦርነት ለመጀመር ከነገ ዛሬ የሚጠብቀውን ኢሳያስን ከኢትዮጵያ በማስታረቅ የአባይን ጉዳይ ውጥረት ለማላላት ሊጠቀሙበት ይሆን ? የሚልው ሌላው የፖለቲካ ተንታኞች ግምት አዘል ጥያቄ ነው፡፤በእርግጥ ኤርትራም ከአባይ ተፋሰስ ሃገሮች ውስጥ አብራ የምትቆጠር ቢሆንም ለአባይ ከምታበረክተው ባዶ አስተዋጾ አንጻር ሙባረክና ኢሳያስን ያተነጋገሩት ከአባይ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ነው የሚለውን ግምት ባዶ ያደርገዋል።

በመጨረሻም ወያኔ  ከህዝብ ጀርባ ተፈራርሞ የህዝብን ጥቅም አሳልፎ በመስጠት በአልጀሪያ ያደረገውን አይነት ክህደት ዛሬ አይደግመውም የሚባል ድርጅት አይደለምና ;የኢትዮጵያ ህዝብ የካይሮውን ጉብኝትና የስምምነቱን ሚስጥር  የማወቅ መብቱን ሊጠቀምበት ይገባል እንላለን፡፤በዚህ ረገድ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ብዙ ይጠበቃል።